ኦጦ

ማርኩስ ሳልዊዩስ ኦጦ ለአጭር ዘመን ለ፫ ወር ከጥር ወር 61 ዓም ጀምሮ የሮሜ መንግሥት ቄሣር ነበር። የአራቱ ቄሣሮች ዓመት ሁለተኛው ንጉሥ ነበረ።

ኦጦ በ24 ዓም በጣልያን ተወለደ። በሮሜ ግቢ፣ ነጉሥ ኔሮን እንደ ጎበዝ ወጣት ቆጠረው። ኔሮን ግን ሚስቱን ከቃመ በኋላ ኦጦን ወደ ሉሲታኒያ (ፖርቱጋል) እንደ አገረ ገዥ ላከው።

የጋሊያ ሉግዱኔንሲስ (ፈረንሳይ) እና የሂስፓኒያ ታራኮኔንሲስ (ስፔን) ክፍላገራት አገረ ገዦች በአመጽ ሲነሡ ኦጦም ከጸረ-ኔሮን ወገን ጋራ ተባበረ። ኔሮን ራሱን ከገደለ በኋላ የሂስፓኒያ አገረ ገዥ ጋልባ ቄሣር ሆነ።

Othon pièce
የኦጦ መሀለቅ

በጥር ወር 61 ዓም የጌርማኒያ ሥራዊት በጋልባ ላይ አመጹበትና የጌርማኒያ አገረ ገዥ ዊቴሊዩስ ንጉሥ እንዲሆን አዋጁ። ጋልባ በሮሜ ቆይቶ አልጋ ወራሹ ሉኪዩስ ካልፒኒዩስ ፒሶ እንዲሆን ሰየመው። በዚህ ኦጦ በተለይ ተናደደ፣ አልጋ ወራሽነቱን ለራሱ መኝቶ ነበርና። የሮሜ ሥራዊት ደግሞ ኦጦን ደገፈውና በጋልባ ላይ አመጹ። ጋልባ በድካምነቱ በቃሬዛ ተሸክሞ ሲቀርብላቸው ገደሉትና ያንጊዜ ኦጦ ለአጭር ወራት በፈንታው የሮሜ ቄሣር ሆነ። መልኩ ለኔሮን ተመሳሳይነት ስለነበረው በሮሜ ዜጎች መኃል እንደ አዲሱ ኔሮን ተወደደ። የኔሮንም ሰዶማዊ «ባል» ስፖሩስ ለራሱ «አገባ»።

ከዚያ ኦጦ የጋልባን ሰነዶች አንብቦ የዊቴሊዩስ ሥራዊት ከጌርማኒያ ቶሎ እንደሚደርስ ተረዳ። የዊቴሊዩስ ወገን ወደ ጣልያን ገብቶ አሸንፎም ኦጦ ብሔራዊ ጦርነት እንዳይስፋፋ እንደ ኔሮን ራሱን እንደ ገደለ ይባላል። ስለዚህ በፈንታው ዊቴሊዩስ በሚያዝያ የሮሜ ቄሣር ሆነ።

Oth001
ኦጦ የሮሜ ቄሣር
አንደማንቱኑም

አንደማንቱኑም ወይም አንደማቱኑም በሮሜ መንግሥት ዘመንና ከዚያ በፊት በኬልቶች መካከል የሊንጎናውያን ዋና ከተማ የአሁኑም ላንግረ ስያሜ ነበር። ይህ ስም በፔውቲንገር ሠንጠረዥና በሌሎች የጥንት መልካምድር ምንጮች ይጠቀሳል።

በኬልቶች ቋንቋ የስሙ ትርጉም «ከወንዛፍ በታች» (ከ«አንዴ-» በታችና «ማንቶ»- አፍ) እንደ መጣ ይመስላል። ሆኖም «-ማቱኑም» የሚል አጻጻፍ ትክክለኛ ቢሆን፣ ፪ኛው ሥር ምናልባት ማቱ («ጥሩ» ወይም «ድብ») ሊሆን ይችላል።

አካባቢው ወደ ሮሜ መንግሥት የተጨመረው በዩሊዩስ ቄሣር ዘመቻዎች ነበር። በሮሜ ንጉሥ አውግስጦስ ዘመን (35 ዓክልበ.-6 ዓ.ም.) ስሙ ከ«አንደማንቱኑም» ወደ «ሊንጎኔስ» (ከኗሪዎቹ ሊንጎናውያን ስያሜ የተነሣ) ተቀየረ። መጀመርያ ከተማው ለጋሊያ ሉግዱነንሲስ ክፍላገር ተያያዘ፤ ከዚያም ወደ ጋሊያ ቤልጊካ ክፍላገር ተጨመረ። በንጉሥ ዶሚቲያኑስ ዘመን ለጊዜ ወደ ጌርማኒያ ክፍላገር ተጨመረ፣ ከዚያም ወደ ሉግዱነንሲስ ተመለሰ።

የከተማው ኗሪዎች ቁጥር ምናልባት እስከ ፰ ሺህ ድረስ በዛ። በ፫ናው ክፍለ ዘመን ከደረሱት ሁከቶች የተነሣ ከተማ በግድግዳዎቹ ውስጥ ተሸሸገ። በሮማውያን ዘመን ከነበሩት ታላቅ ቤቶች ወይም መዋቅሮች አንዳንድ ለሥነ ቅርስ ታውቋል። በከተማው ዙሪያ የሸክላ፣ የድንጋይ እና የብረታብረት ሠሪዎች እንደ ተገኙ ይታወቃል። ከከተማው ውጭ ደግሞ አራት መቃብር ቦታዎች ወደየአቅጣጫው ተገኝተዋል።

ከተማው በዋና መንገዶች መሸጋገሪያ ላይ በመቀመጡ አይነተኛ ሚና ይጫወት ነበር። ከልዮን ወደ ትሬቭ የሚወስደው የአግሪፓ መንገድ በአንደማንቱኑም በኩል ሲያልፍ፣ በተጨማሪ ወደ ደቡብ ወደ በሳንሶንና ወደ ስሜን ወደ መትዝ የሚሄድ መንገድ ነበር። ሌላ መንገድ ደግሞ ወደ ስሜን-ምዕራብ ወደ ሬም ሄደ።

ታኪቱስ እንደሚጽፈ፣ በጨካኙ ንጉሥ ኔሮን ዘመን አንዳንድ ሰዎች በአመጽ ሲነሡ ሊንጎናውያን ግን ያንጊዜ አልተሳተፉም። ኔሮ ከተወገደ በኋላ፣ ተከታዩ ጋልባ በአመጹ ያልተሳተፉት ነገዶች ከነሊንጎናውያን በቂም ቀጣቸው። በቅርብ ጊዜ ሌላ አለቃ ኦጦ ጋልባን ገድሎ ዙፋኑን ያዘ። ሊንጊናውያን ግን በዚህ ትግል ሌላ አለቃ ዊቴሊዩስ ደገፉ። ይህ «የአራት ነገሥታት ዓመት» (62 ዓ.ም.) ይባላል፤ በመጨረሻም ዌስፓሲያኑስ አሸነፈና ንጉሡ ሆነ።

ነገር ግን ያንጊዜ የሊንጎናውያን ብሔር እንደገና ሌላ ሰው መሪያቸውን ዩሊዩስ ሳቢኑስ ለሮሜ ንጉሥነት ደገፉ። የጋሊያ ከተሞች ማኅበር በዱሮኮርቶሩም (ሬም) ተሰብስቦ ዓመጽ እንዲተውና ሰላም እንዲሆን መረጡ። ሳቢኑስ ስለዚህ ቤቱን አቃጥሎ ከከተማው ከሚስቱ ኤፖኒን ጋራ እንዲሸሽ ተገደደ፣ ለ፲ም አመታት በዋሻ ይጠጉ ነበር። ሰላማዊ በሆነበት ወቅት፣ ሳቢኑስና ኤፖኒን የዌስፓሲያን ይቅርታ ለመለመን ወደ ሮሜ ተጓዙ። ንጉሡ ግን እምቢ ብሎ ሁለቱን አስገደላቸው።

ከ250 ዓ.ም. ጀምሮ ፍራንኮች በዶሮኮርቶሩም (ሬም) እና አለማኒ በሉግዱኑም (ልዮን) ያስቸግሩት ነበር። ላንግረ ከነዚህ ቦታዎች መካከል በመሆን ሁለቱ ሠራዊቶች ያጠፉት ነበር። በ290 ዓ.ም. ግን ንጉሡ ኮንስታንቲዩስ የአለማኒ ጎሣ እዚህ በሊንጎኔስ ውግያ አሸነፋቸው። እንደ ትውፊቱ ንጉሡ በመጀመርያ ወደ ከተማው መሸሽ ሲሞክር፣ በሮቹ ግን ተዘግተው ስለ ሆኑ በገመዶች አማካይነት ከግድግዳው በላይ ማረግ እንደ ነበረበት ይባላል። ከዚያ የታደሰው ሥራዊት ከከተማው ወጥተው ምናልባት እስከ ፷ ሺህ ጠላቶች አጠፉ።

ዊቴሊዩስ

አውሉስ ዊቴሊዩስ ለአጭር ዘመን ለ፰ ወር ከሚያዝያ ወር 61 ዓም ጀምሮ የሮሜ መንግሥት ቄሣር ነበር። የአራቱ ቄሣሮች ዓመት ሦስተኛው ንጉሥ ነበረ።

ዊቴሊዩስ በ7 ዓም በጣልያን ተወለደ። በካፕሪ ደሴት ግቢ፣ ነጉሥ ቲቤርያስ እንደ ጎበዝ ልጅ ቆጠረው፣ እንዲሁም ለሰዶማውያን ነገሥታት ካሊጎላና ኔሮን ተወዳጅ ነበረ።

ኔሮን ዓርፎ ጋልባ ቄሣር እንደ ሆነ፣ ዊቴሊዩስ የጌርማኒያ አገረ ገዥ አድርጎ ሾመው። በጌርማኒያ ግን ሥራዊት በጋልባ ላይ አመጸና ዊቴሊዩስ ቄሳር ተብሎ አወጁት።

የጋሊያ (ፈረንሳይ)፣ ብሪታኒያና ራይቲያ (ስዊስ) ክፍላገራት ሥራዊት ደግሞ ዊቴሊዩስን ደገፉ። ስራዊቶቹ በጣልያን ደርሰው ግን በጋልባ ፈንታ ኦጦ ቄሣር ሆኖ አገኙት። ኦጦ በቀላል ተሸነፈና ዊቴሊዩስ ቄሣር ሆነ። በይፋ «ቄሣር» በሚለው ማዕረግ ፈንታ አዲስ ማዕረግ «ጌርማኒኩስ» ተባለ። እንደ ቅድመኞቹ ጨካኝና መረን ፈላጭ ቁራጭ ነበር፣ ብዙ ሰዎች ለደስታው ገደለ። በተጨማሪ የታሪክ ጸሐፊዎች እንደሚሉ እጅግ ሆዳም ሰው ነበር፣ አራት ጊዜ በየቀኑ ታላቅ ግብዣ በቅንጦት ይበላ ነበር።

ከጥቂት ወራት በኋላ በሐምሌ 61 ዓም፣ የምሥራቅ ክፍላገሮች ስራዊቶች አለቆቻቸውን ቤስጳስያን እንደ ቄሣር በአመጽ ሾሙት። ይህ የሞይስያ፣ ፓኖኒያ፣ ሶርያ እና ይሁዳ ክፍላገራት ሥራዊት ለቤስጳስያን የደገፉት ነው። በታህሳስ ወር 62 ዓም. የቤስጳስያን ወገን ሲያሸንፍ ዊቴሊዩስ ራሱን ለመደብቅ ሲሞክር፣ በቤስጳስያን ሥራዊት ተገኝቶ ተገደለ። ቤስጳስያንም ያንጊዜ ቄሣር ሆኑ።

የአራቱ ቄሣሮች ዓመት

የአራቱ ቄሣሮች ዓመት በሮሜ መንግሥት ታሪክ አራት ቄሣሮች በየተራቸው የተነሱበት ዓመት ወይም 69 እ.ኤ.አ. ነበር። እነኚህም አራት ቄሣሮች ጋልባ፣ ኦጦ፣ ዊቴሊዩስና ቤስጳስያን ናቸው። በኢትዮጵያ አቆጣጠር የነባሩ ቄሣር ኔሮን ራሱን ከገድለበት ወቅት ከሰኔ ወር 60 ዓም ጀምሮ ቤስጳስያን እስካሸነፈበት ወቅት እስከ ታኅሳስ 62 ዓም ድረስ የነበረው ብሔራዊ ጦርነት ማለት ነው።

1. ጋልባ - ፯ ወር ቆየ - በሰኔ 60 ዓም በኔሮን ያመጹ ክፍላገራት፦ ጋሊያ፣ ሂስፓኒያ

2. ኦጦ - ፫ ወር ቆየ - በጥር 61 ዓም የሉሲታኒያ አገረ ገዥ ሲሆን ከሮሜ ሥራዊት ጋር በጋልባ አመጸ

3. ዊቴሊዩስ - ፰ ወር ቆየ - በጥር-ሚያዝያ 61 ዓም በኦጦ ያመጹ ክፍላገራት፦ ጌርማኒያ፣ ጋሊያ፣ ራይቲያ፣ ብሪታኒያ

4. ቤስጳስያን - ከሐምሌ 61-ታህሳስ 62 ዓም በዊቴልዩስ ያመጹ ክፍላገራት፦ ሶርያ፣ ይሁዳ፣ ግብጽ፣ ሞይስያ፣ ድልማጥያ፣ ፓኖኒያ

ጋልባ

ሴርዊዩስ ሱልፒኪዩስ ጋልባ ለአጭር ዘመን ለ፯ ወር ከሰኔ ወር 60 ዓም ጀምሮ የሮሜ መንግሥት ቄሣር ነበር። የአራቱ ቄሣሮች ዓመት መጀመርያው ንጉሥ ነበረ።

ጋልባ በ10 ዓክልበ. በጣልያን ተወለደ። በሮሜ ግቢ፣ ነገሥታት አውግስጦስና ጢቤርዮስ እንደ ጎበዝ ወጣት ቆጥረውት ወደ ፊት ትልቅ ይሆናል እንዳሉ ተጽፏል። በነገሥታት ሰዶማዊ ኑሮ ዘዴ ልጆች አልወለዱም ስለ ነበር፣ አልጋ ወራሽ ምንጊዜም የተወደደው ጎረምሳ እንደ ንጉሥ ዕንጀራ ልጅ ነበር።

ጋልባ በ12 ዓም በሥራዊት የፕራይቶር ማዕረግ አገኘ፣ ለ25 ዓም ቆንሱል ሆኖ ተመረጠ። በ53 ዓም ንጉሥ ኔሮን የሂስፓኒያ ታራኮነንሲስ ክፍላገር (ምሥራቅ ስፔን) አገረ ገዥ አድርጎ ሾመው።

የጋሊያ ሉግዱኔንሲስ (ፈረንሳይ) አገረ ገዥ ጋዩስ ዩሊዩስ ዊንዴክስ በኔሮን ማባከንና አምባገነንነት ተቀይሞ በ60 ዓም ዓመጸበት። በኔሮን ፈንታ ጋልባ የተሻለ ቄሣር ለማድረግ አሰበ። የኔሮን ጌርማኒያ ሥራዊት አለቃ ሉኪዩስ ዌርጊኒዩስ ሩፉስ ግን በውግያ ዊንዴክስን አጠፋው። ከዚህ በኋላ የዌርጊኒዩስ ሥራዊት እሱን በኔሮን ፈንታ ይደግፍ ነበር፤ ዌርጊኒዩስ ግን የትም አልገሠገሠም። ጋልባ ከኔሮ ይሻለናል የሚል ስሜት ከፈረንሳይና ከስፔን ይልቅ ወደ ጣልያን እራሱ ሲስፋፋ፣ የኔሮን ሥልጣን እየጠፋ፣ በመጨረሻ ኔሮን ራሱን ገደለና ጋልባ ወደ ሮሜ ገሥግሦ ወዲያው ቄሣር ተደረገ።

ከዚህ ብሔራዊ ትግል ቀጥሎ ጋልባ የማይቀበሉትን ብዙ ገደለ፤ ወይም በገብር ሸከማቸው፤ በአጠቃላይ ጨካኝ አመራር ተከተለ። በእርጅናው ደግሞ ሦስት ወንድ ተወዳጆች በእውነት እንደ ገዙት ይባል ነበር።

በሚከተለው ጥር ወር የጌርማኒያ ሥራዊት በጋልባ ላይ አመጹበትና የጌርማኒያ አገረ ገዥ ዊቴሊዩስ ንጉሥ እንዲሆን አዋጁ። ጋልባ በሮሜ ቆይቶ አልጋ ወራሹ ሉኪዩስ ካልፒኒዩስ ፒሶ እንዲሆን ሰየመው። በዚህ የሉሲታኒያ (ፖርቱጋል) አገረ ገዥ ኦጦ በተለይ ተናደደ፣ አልጋ ወራሽነቱን ለራሱ መኝቶ ነበርና። የሮሜ ሥራዊት ደግሞ ኦጦን ደገፈውና በጋልባ ላይ አመጹ። ጋልባ በድካምነቱ በቃሬዛ ተሸክሞ ሲቀርብላቸው ገደሉትና ያንጊዜ ኦጦ ለአጭር ወራት በፈንታው የሮሜ ቄሣር ሆነ።

በሌሎች ቋንቋዎች

This page is based on a Wikipedia article written by authors (here).
Text is available under the CC BY-SA 3.0 license; additional terms may apply.
Images, videos and audio are available under their respective licenses.