ኦሪት ዘኊልቊ

ኦሪት ዘኊልቊመጽሐፍ ቅዱስ ብሉይ ኪዳንና በኦሪት አራተኛው መጽሐፍ ነው። ሙሴ እብራውያንን ከሲና ልሳነ ምድር እስከ ከነዓን ጠረፍ ድረስ ሲመራቸው ይተርካል። በዚህ ውስጥ ያሉት ሕግጋት ወይም ትአዛዛት በሕገ ሙሴ ውስጥ ይቆጠራሉ።

አቫሪስ

አቫሪስ (ግሪክኛ፦ Αυαρις /አዋሪስ/፣ ግብጽኛ፦ ሑት-ዋረት፣ ሐዋረት) ጥንታዊ የግብጽ ከተማ ነበረ።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ «ጣኔዎስ» ወይም «ጣይናስ» በአብርሃም ዘመን ከኬብሮን 7 ዓመታት በኋላ መሠራቱን ሲያመለከት (ኩፋሌ 11:23፣ ኦሪት ዘኊልቊ 13፡22)፣ የዚሁ አቫሪስ ሥፍራ ማለት ሳይሆን አይቀርም። በሂክሶስ ዘመን የሂክሶስ ዋና ከተማ ሆነ። በኋላ (1548 ዓክልበ. ግድም) የግብጽ ኗሪ 18ኛው ሥርወ መንግሥት ፈርዖን 1 አህሞስ አቫሪስን ይዞ የሂክሶስ ወገን ከግብጽ አውጥቶ ወደ እስያ (ከነዓን) እንደ መለሳቸው ይመስላል። በ19ኛው ሥርወ መንግሥት በአቫሪስ አጠገብ አዲስ ዋና ከተማ ፒ-ራምሴስ ተሠራ።

እንበረም

እንበረም (ዕብራይስጥ፦ ዐምራም፣ አረብኛ፦ ዒምራን) በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት የሙሴ፣ የአሮንና የማርያም አባት ነበረ። ኦሪት ዘጸአት ስለ እንበረም ጥቂት መረጃ ቢገኝም፣ በመጽሐፈ ኩፋሌ፣ በቁራንና እንዲሁም በሌሎች ምንጮች ተጨማሪ ልማዶች አሉ።

ኪቲም

ኪቲም (ዕብራይስጥ፦ כִּתִּים) በኦሪት ዘፍጥረት 10 መሠረት ከያዋን ልጆች አንዱ ነበር። እንዲሁም ከእርሱ የተወለደው ብሔርና አገራቸው «ኪቲም» ይባላሉ።

ካሌብ

ካሌብ በብሉይ ኪዳን ውስጥ የእስራኤል ሰው ነበረ። ከግብፅ ከጥልቅ ጭቆና ባርነት ከወጡ 603,550 ያህል ወንዶችና ቤተሠቦቻቸው ሁሉ መካከል እርሱና ኢያሱ ወልደ ነዌ ብቻ ዮርዳኖስ ወንዝን በመሻገር ወደ ከነዓን በሕይወት እንዲገቡ ተፈቀዱ። ይህ የሆነው ኢያሱና ካሌብ በመንፈሳቸው ለእግዚአብሔር ስለ ታዘዙ ነው። ከግብጽ ያመለጡት ሌሎች ሁሉ በሲና ምድረ በዳ ዙሪያ ለ40 ዓመታት ቆይተው 601,730 ልጆቻቸው ወደ ከነዓን የዘመቱ ናቸው እንጂ ትውልዳቸው በሙሉ በ40 ዓመታት ውስጥ አልቀሩም።በፕሲውዶ-ፊሎ ዘንድ ወንድሙ ቄኔዝ ከኢያሱ ቀጥሎ የእስራኤል ፈራጅ ሆነ።

ዐግ

ዐግ (ዕብራይስጥ עוֹג /ዖግ/) በብሉይ ኪዳን ዘንድ እስራኤላውያን በሙሴ መሪነት በኤድራይ ውጊያ እስካሸነፉት ድረስ (ምናልባት 1621 ዓክልበ.) የባሳን አገር (በአሁን ዮርዳኖስ) አሞራዊ ንጉሥ ነበር።

መጀመርያ ሲጠቀስ ኦሪት ዘኊልቊ እንደሚገልጽ፣ ይህ ውግያ ሌላውን አሞራዊ የሐሴቦን ንጉስ ሴዎንን ካሸነፉት ቀጥሎ ሆነ።

«ተመልሰውም በባሳን መንገድ ወጡ፤ የባሳንም ንጉሥ ዐግ ከሕዝቡ ሁሉ ጋር በኤድራይ ይወጋቸው ዘንድ ወጣ። እግዚአብሔርም ሙሴን፦ እርሱንና ሕዝቡን ሁሉ ምድሪቱንም አሳልፌ በእጅህ ሰጥቼአለሁና አትፍራው፤ በሐሴቦንም በተቀመጠው በአሞራውያን ንጉሥ በሴዎን እንዳደረግህ እንዲህ ታደርግበታለህ አለው። እርሱንና ልጆቹን ሕዝቡንም ሁሉ መቱ ሰውም አልቀረለትም፤ ምድሩንም ወረሱ።» ኦሪት ዘኊልቊ 21:33-35ተመሳሳይ ዐረፍተ ነገሮች እንደገና በኦሪት ዘዳግም 3:1-3 ይደገማሉ፣ ከዚያም እንዲህ ይቀጠላል፦

«በዚያን ጊዜም ከተሞቹን ሁሉ ወሰድን፣ አንድም ያልወሰድነው የለም፤ በባሳን ያለውን የዐግን መንግሥት፥ የአርጎብን አገር ሁሉ፥ ስድሳ ከተሞችን ወሰድን። በቅጥር ካልተመሸጉት ከእጅግ ብዙ ከተሞች ሌላ፥ እነዚህ ከተሞች ሁሉ ቁመቱ ረጅም በሆነ ቅጥር በመዝጊያና በመወርወሪያም የተመሸጉ ነበሩ። ...

«በዚያም ዘመን ከአርኖን ሸለቆ ጀምሮ እስከ አርሞንኤም ተራራ ድረስ ምድሪቱን በዮርዳኖስ ማዶ ከነበሩት ከሁለቱ ከአሞራውያን ነገሥታት እጅ ወሰድን... በሜዳውም ያሉትን ከተሞች ሁሉ፥ ገለዓድንም ሁሉ፥ በባሳንም ያሉትን የዐግን መንግሥት ከተሞች እስከ ሰልካና እስከ ኤድራይ ድረስ ባሳንን ሁሉ ወሰድን። ከራፋይም ወገን የባሳን ንጉሥ ዐግ ብቻውን ቀርቶ ነበር፤ እነሆ፥ አልጋው የብረት አልጋ ነበረ፤ እርሱ በአሞን ልጆች አገር በረባት አለ፤ ርዝመቱ ዘጠኝ ክንድ ወርዱም አራት ክንድ በሰው ክንድ ልክ ነበረ። »

«ራፋይም» ደግሞ በኦሪት ዘንድ በሎጥ ዘመን ከዮርዳኖስ ምሥራቅ የተገኘ ወገን ሲሆን (ዘፍጥረት 14:5)፣ በሗላ ከሎጥ የተወለዱት ብሔሮች አሞናውያንና ሞአብ አገራቸውን ያዙ (ዘዳግም 2:9, 19, 22)። ሞአባውያን እነዚህን ሰዎች «ኤሚም» ሲሉዋቸው (ዘዳግም 2:10)፣ አሞናውያንም «ዘምዙማውያን» (ዘዳግም 2:20) ይሉዋቸው ነበር። እንዳጋጣሚ ዕብራይስጡ ስማቸው «ራፋይም» በሌላ ሥፍራ «የሙታን ጥላዎች» ይተረጎማል፤ የብሔሩም ትክክለኛ ስም «የዔናቅ ልጆች» እንደ ሆነ፣ «በቁመት የረዘሙ» እንደ ሆኑ በዘዳግም 2:10-11 ይገለጻል። የዔናቅም ልጆች በዘኊልቊ 13:33 «የኔፊሊም ወገን» ይባላሉ። ሆኖም በዘፍጥረት 6:4 «ኔፊሊም» በማየ አይኅ የጠፋ ወገን መሆኑ ግልጽ ስለ ሆነ ሐረጋቸው ከነዚህ ቅድመኞቹ «ኔፊሊም» ሊሆን አይቻልም።

ቢሆንም፣ በሗለኞቹ አይሁድና እስልምና ትውፊቶች ዘንድ፣ ይሄ ንጉሥ ዐግ «ከራፋይም ወገን» ሲሆን የኖህ መርከብን በመያዝ ከጥፋቱ ውሃ ለማምለጥ የቻለ በጣም ረጅም ሰው ነበረ። ነገር ግን ይህ በተልሙድ የተመዘገበ ትውፊት የዐግ እድሜ በመገደሉ ከአንድ ሺህ አመታት በላይ ያድርገው ስለ ሆነ ከተለመደው ዜና መዋዕል ጋር ልክ አይሆንም። በሃዲስና በሌሎች እስላማዊ ጽሑፎች ስሙ «ዑጅ ኢብን ዓናቅ» ሲባል እናቱ ደግሞ «ዓናቅ ቢንት አዳም»፣ የአዳም ልጅና የቃየል ክፉ እኅት፣ ተባለች። ስለ «ኡንጁ ቢን ኡኑቅ የሆኑ ተጨማሪ ትውፊቶች በታንዛኒያ ተገኝተዋል፣ ቁመቱም አንድ ማይል እንደ ረዘመ ይላሉ።

በአይሁዶች ባቢሎን ተልሙድ ዘንድ ዐግና ሴዎን ሁለቱ የኦሕያስ ወይም ኦጊያስ ልጆች፣ ኦሕያስም የሰምያዛ (የትጉሃን አለቃ በመጽሐፈ ሄኖክ) ልጅ እንደ ነበር ይላል። በቁምራን የተገኘው «የረጃጅሞች መጽሐፍ» ደግሞ ዘንዶ የገደለውን ኦሕያስንና ሰምያዛን ጠቅሶዋል፣ ያውም ጽሑፍ በኋላ ለማኒኪስም እምነት ይታወቅ ነበር። ዳሩ ግን ከነዚህ ትውፊቶች ውጭ በትክክለኛ መጽሐፍ ቅዱስ ቅደም-ተከተል በኖኅ መርከብ ካሉት ስምንት ሰዎች ብቻ በስተቀር አንዳችም ሰው ዘርን እንዳላተረፈ ግልጽ ነው። ስለዚህ በ1621 ዓክልበ. ገደማ የተገደለው የባሳን ንጉሥ ዐግ ከአሞራዊ (ከነዓን) ወገን ነበር የሚለው መረጃ ትክክል ይመስላል።

የዐግ ታላቅ አልጋ በረባት በአሞን አገር ተገኘ ሲል ይህ ከተማ ዘመናዊ አማን፣ ዮርዳኖስ ነው፤ በዚያም ለዚሁ ትልቅ መጠን የሆነ የድንጋዮች ቅርጽ ለሥነ ቅርስ ይታወቃል።

የበለዓም ጽሑፍ

የበለዓም ጽሑፍ በሥነ ቅርስ በ1960 ዓ.ም. በዴር አላ፣ ዮርዳኖስ የተገኘ ጽሑፍ ነው። ጽሑፉ አራማያ በሚመስል ቋንቋ ሲሆን የቢዖር ልጅ በለዓም የነበየ ትንቢት ይናገራል።

ይህ አረመኔ ነቢይ በመጽሐፍ ቅዱስ በተለይም ኦሪት ዘኊልቊ ምዕ. 22-24 ስለሚጠቀስ፣ በሙሴና በኢያሱ ዘመን እንደ ኖረ ስለሚባል፣ ይህ ጽሑፍ ለሊቃውንቱ ዕጅግ በጣም ቁም ነገር ይሆን ነበር። ይሁንና በብሉይ ኪዳን ከንጉሥ ዳዊት አስቀድሞ ለነበሩት ሰዎች አንዳችም ቅርስ የለም በማለት ብዙዎቹ ስለሚያስመስሉ፣ በአብዛኛው ቸል ብለውታል። ስለዚህ ታዋቂነቱ በደንብ ገና አልተስፋፋም። በጠቀሱት ጥቂት ሊቃውንት አስተሳሰብ ዘንድ፣ ጽሁፉ 840 ዓክልበ. ግድም ተሳለ።

የጽሑፉ ቃላት በቀይና በጥቁር ቀለሞች በአንድ ግድግዳ ላይ ተቀለሙ። ከምድር መንቀጥቀጥ የተነሣ ይህ ግድግዳ ፍርስራሽ ሆኖ ጽሑፉ በሙሉ ሊተረጎም ባይቻልም፣ ትልቁ ክፍል ግን ተተረጎማል። ትንቢቱም በመጨረሻው ዘመን ስለሚደርሰው የዓለም ጥፋት ነው። ትንቢቱ ለበለዓም የመጣው ከ«ኤሎሂም» ነው ሲል፣ ይህ ግን በሊቃውንቱ ሀሳብ ዘንድ እንደ ዕብራይስጥ «አምላክ» ማለት ሳይሆን፣ ማለቱ በብዙ ቁጥር «አማልክት» መሆን አለበት ይላሉ።

የበለዓም ጽሑፍ ከነትርጉሙ በእንግሊዝኛ

የፋራን ምድረ በዳ

የፋራን ምድረ በዳ (ዕብራይስጥ מדבר פארן /ሚድባር ፓእራን/) በመጽሐፍ ቅዱስ የሚጠቀስ ቦታ ነው።

ስሙ መጀመርያ የሚታየው በኦሪት ዘፍጥረት 14፡6 ሲሆን፣ የኤላም ንጉሥ ኮሎዶጎምርና ከሱ ጋር ሌሎቹ ነገሥታት «የሖር ሰዎችንም በሴይር ተራራቸው በበረሀ አጠገብ እስካለች እስከ ኤል ፋራን ድረስ መቱ።» ከዚህ የፋራን ሥፍራ በሰዶምና ገሞራ አካባቢ እንደ ተገኘ ይመስላል። የአብርሃም በኲር ልጅ እስማይል እና እናቱ ሀጋር ከቤርሳቤ ከተሰደዱ በኋላ በፋራን መኖርያ አገኙ።

በኋላ በሙሴ ዘመን የእስራኤል ልጆች ከግብጽና ከከነዓን መካከል ለ40 ዓመት ሲቆዩ፣ ከሠፈሩባቸው ምድረ በዳ ቦታዎች መካከል ይቆጠራል (ኦሪት ዘኊልቊ 10:12)። በኦሪት ዘዳግም 1:1 እንደገና፣ «በዮርዳኖስ ማዶ በምድረ በዳ፥ በዓረባ ውስጥ በኤርትራ ባሕር ፊት ለፊት፥ በፋራን በጦፌልም በላባንም በሐጼሮትም በዲዛሃብም መካከል ሳሉ፥ ሙሴ ለእስራኤል ሁሉ የነገራቸው ቃል ይህ ነው» በማለት ይጀመራል። በኋላ በምዕራፍ 33 ደግሞ «እግዚአብሔር ከሲና መጣ፥ በሴይርም ተገለጠ፤ ከፋራን ተራራ አበራላቸው...» የሚልን በረከት እናነባለን።

እንደገና በዳዊት ጊዜ ዳዊት በፋራን ምድረ በዳ ሸሸገ (1 ሳሙኤል 25፡1)። በተጨማሪ በ1 ነገሥታት 11:17-18 ዘንድ የኤዶምያስ ሰው ሃዳድ ከኤዶምያስ ወደ ግብጽ በሸሸበት ወቅት፣ በምድያምና በፋራን አገሮች እንዳለፈ ይነግራል።

ከነዚህ ጥቅሶች ሁሉ የተነሣ ብዙ ጊዜ ይህ ምድረ በዳ በሲና ልሳነ ምድር ውስጥ ወይም እስከ ዮርዳኖስ ጨው ባሕር ድረስ ያለው ምድረ በዳ መሆኑ ይታስባል።

በሌላ ልማድ ግን የፋራን ሥፍራ በመካ (በአሁኑ ሳዑዲ አረቢያ) ዙሪያ ነበር የሚል አስተሳሰብ አለ። በተለይ በእስልምና እስማይልና ሀጋር ስደት ያገኙበት አገር ፋራን በመካ ዙሪያ ነበር። በዚህ ትምህርት «ፋራን» ማለት ሄጃዝ ወይም ምዕራቡ አረቢያ ነው። በመካ አካባቢ የተገኙ ኮረብቶች ወይም ተራሮች «የፋራን ተራሮች» እንደ ተባሉ የሚሉ አንዳንድ ጥንታዊ ምንጮች አሉ።

በሌሎች ቋንቋዎች

This page is based on a Wikipedia article written by authors (here).
Text is available under the CC BY-SA 3.0 license; additional terms may apply.
Images, videos and audio are available under their respective licenses.